ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አንድ ሌዝቢያን የምኖረውን በደስታ የተሞላ ህይወት ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።
ባለቤቴን ያገኘሁት በኢትዮጵያ በኩዊር ማህበረሰብ ላይ ያለው ጥላቻ በከፋ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። እርስ በርስ የመገናኘትን አደጋ ለመውሰድ ከመወሰናችን በፊት ከአንድ ወር በላይ ተነጋገርን። ቃላቶቿን የመረጠችበት እና የምታስተካክልበት መንገድ በጣም አስደነቀኝ እና ሀሳቦቿ እና አስተሳሰቧ በጣም አስገረሙኝ። ተመሳሳይ የአስተሳሰብ መንገድ እና ቀልደኛነት እንኳን ያለን መስሎ ቢሰማኝም እኔ ግን ለራሴ “ቆይ ምናልባት ይህ የፌስቡክ ስብዕናዋ ብቻ ሊሆን ይችላል” ብዬ ሁሉ ነግሬው ነበር። ምናልባት እሷ በእውነቱ በአካል እንደዚህ አይነት ሰው አይደለችም፤ ምናልባት ይህ የእሷ የማህበራዊ ሚድያ ስብዕና ሊሆን ይችላል” ብዬ አስቤ ነበር።
ከዚያም ለመገናኘት ወሰንን። እናም በእውነት ምንም ቅር አልተሰኘሁም ነበር! እሷ የእኔን ህልሞች እና ተስፋዎች ሁሉ አሟላች። ደስ የሚልና የተረጋጋ ድምፅ ያላት ቆንጆ፣ ረጅም ሴት… መልክዋና ስታይልዋ በጣም አስደነቀኝ – ሰፊ ሱሪ እና ጃኬት። በጥቁር ልብስ ያሸበረቀች ውብ ልጅ።

ከዚያም ማውራት ጀመርን። የመሰልቸት ስሜት ምንም አልተሰማኝም፤ ለሰከንድም እንኳን። እራሴን ብዙ እያወራን እና በውይይቱ በጣም እየተደሰትኩ ነው ያገኘሁት። ይህ ለእኔ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር ነው። እኔ ነገር ቶሎ የሚሰለቸ አይነት ሰው ነኝ ግን ከሷ ጋር ስሆን ይሄ ነገር አልሆነም። በጨዋታችን እየተደሰትኩ ነበር። በኩዊር ማህበረሰባችን ውስጥ ስላሉ ብዙ ነገሮች ተወያይተናል። ያልተሟሉ ዓረፍተ ነገሮቼን ስታጠናቅቅ፣ ሀሳቤን እያደራጀች እና የማስበውን እንኳን ስትናገር አገኘኋት። “ብቻ ምን አለፋቹህ አንድ አይነት ሰው በሉን” (ለማሳጠር ያህል, እኛ አንድ ሰው እንደሆንን ነበር የተሰማን)።
ይህ አባባል ከሁሉም በላይ ይገልፃታል፡ ለኔ በትክክለኛዋ ጊዜ የተገኘች ትክክለኛዋ ሰው ነበረች። በዚያ ቀን እግዚአብሔርን በመቶዎች የሚቆጠሩ ጊዜ አመሰገንኩት። የምፈልገው ነገር በአንድ ሰው ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሰጠኝ። በዚያን ጊዜ አደጋው በእውነት የሚያስቆጭ ነበር።
ዛሬ አብረን እንኖራለን። ከምወዳት ሴት አጠገብ በየቀኑ ከእንቅልፌ እነቃለሁ፣ እና አሁንም በመጀመሪያው ቀን ከእሷ ጋር የተሰማኝን አይነት ስሜት ይሰማኛል። ቀን ከቀን ፍቅሯ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚያድግ ማየት ችያለሁ። የምታደርግልኝ ነገር ፍቅሮን ይናገራል። ተግባሯ ሁሉንም ነገር ነው የሚናገረው። ቁርስን ለማዘጋጀት በማለዳ በምትነቃበት መንገድ፣ ከስራ ስመለስ የተዘጋጀ እራት የማገኝበት መንገድ፣ ሁልጊዜም በጥሩ ሁኔታ እንዴት እንደምትንከባከበኝ ያሳያል። ለእኔ የሚስማማኝን ጤናማ ምግብ ለማዘጋጀት በትኩረት በምትከታተልበት መንገድ እና በሌሎች በርካታ መንገዶች ይገለፃል።
ቲክ ቶክን አብረን እየተመለከትን በቤት ውስጥ አብረን የምናሳልፈውን ቆንጆ ጊዜ ራሱ የፍቅሯ መገለጫ ነው። በቀላሉ ስለማንኛውም ነገር እና ስለ ሁሉም ነገር አብረን ቡና እየጠጣን ማውራት፣ እና ብርድ በሚሆንበት ወቅት ሌሊቱን በአንድ ብርድ ልብስ እቅፍ አድርጋኝ ስለወደፊታ ህይወታችን ስንወያይ ደስ ይለኛል።
ስለእኛ በጣም የምወደው ነገር ካለፈው ይልቅ ወደፊት ላይ ማተኮራችን፣ እቅድ ማውጣት እና ህይወታችን ወደፊት ምን እንደሚመስል እንዴት እንደምናስብ እና የሚያጋጥሙንን ነገሮች ሁሉ ለመቋቋም የምንወያየው ነገር ነው።
አሁን በጣም ደስተኛ ሴት እንደሆንኩ ይሰማኛል። ከእሷ ጋር ያለው ሕይወት በሰላም፣ በፍቅር እና በመግባባት የተሞላ ነው። እና ይህ የምፈልገው ነገር ነው።
እዚህ የኩዊር ማህበረሰብ ውስጥ የህይወትን ትርጉም ተረድተው ሰላማዊ ህይወትን ለማግኘት የሚጥሩ ድንቅ ሰዎች አሉ። በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ያለ ሰዎች የሚፈልጉት ህይወት እንደሚያገኙ ተስፋ አደርጋለሁ።
ከትክክለኛ ሰዎች ጋር ስንሆን ሁላችንም መረጋጋት፣ መወያየት እና ህይወታችን እንደሚያምር ማወቅ እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ።