በአንድ ጊዜ ራሴን አልተቀበልኩም። ኢየሱስ በእኔ ላይ እንደተቆጣ እና ሊቀጣኝ እንደተዘጋጀ በማመን ለረጅም ጊዜ የኃጢአተኛነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ለረጅም ጊዜ አለቀስ ነበር፤ እግዚአብሔርም “ኖርማል” እንዲያደርገኝ ተደፍቼ አጥብቄ እለምነው ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ እግዚአብሔር ወደ የተቀራኒ ፆታ አፍቃሪ ሰው እንዲለውጠኝ ተንበርክኬ በጣም እያለቀስኩኝ ፀለይኩኝ። ከዛም ለራሴ ይህ ስሜቴ ከዚህ በኋላ ካልተቀየረ ይህ የጌታን በረከት አገኘሁ ማለት ነው ብዬ ደመደምኩኝ። ነገሮች ይለወጣሉ ብዬ ተስፋ በማድረግ ትንሽ ታግሼ ጠብቄአለሁ፣ ግን ምንም ነገር አልጠለወጠም፤ ያው ኩዊር ነበርኩ። ያው ስሜቴ አሁንም ለተመሳሳይ ፆታ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደማይሳሳት እና እንደ እኔንም ፍፁም ትክክል አርጎ እንደፈጠረኝ ያኔ ነው የተረዳሁት።

ከጥቂት አመታት በፊት ራሴን ከተቀበልኩ በኋላ፣ ሌሎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ በማሰብ አሁንም ራሳቸውን ለመቀበል ሲታገሉ ሳይ እገረማለሁ። ለሁለት ወይም ለሦስት ዓመታት በፍቅር ግንኙነት ውስጥ የቆዩ ጓደኞች አሉኝ፣ ሆኖም ግን አሁንም እግዚአብሔር ከማንነታቸው እንዲያድናቸው ይጠብቃሉ፤ ማንነታቸው ጊዜያዊ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ማንነታቸውን ለመቀበል ከእግዚአብሔር የፁሑፍ መልእክት እየጠበቁ እንደሆነ በማሾፍ እየጠየቁ ከእነርሱ ጋር እቀልዳለሁ። ሲታገሉ ማየት በጣም ያሳዝናል፣ እና ምንም ያህል ማንነታቸው ችግር እንደሌለው ላረጋግጥላቸው ብሞክርም እነሱ አያምኑኝም። በርግጥ እኔ ሙሉ በሙሉ እረዳቸዋለሁ ምክንያቱም እኔም ተመሳሳይ ስሜት ነበረኝ። የእራሴን ማንነት እንድቀበል የሚመክሩኝን ሰዎች አልሰማም ነበር። ከአንድ ሰው ጋር አንሶላ በተጋፈፍኩኝ ቁጥር የቆሻሻነት ስሜት ይሰማኝ ስለነበር በተቃራኒ ጾታ ለመሳብ ራሴን ለማስገደድ በጣም ሞከርኩ፣ ግን ምንም ነገር አልሰራም።
ራሴን እንዴት መቀበል እንዳለብኝ እና ኩዊር መሆኔ ምንም ችግር እንደሌለው ለመገንዘብ ራሴን ማስተማር ነበረብኝ። ጓደኞቼ ራሳቸውን ለመቀበል ያሉበትን ውዝግብ እና ጥርጣሬ ሲያካፍሉኝ እና ጭንቀታቸውን ለማቃለልም ሲቀልዱ አዳምጣለሁ፣ነገር ግን አሁንም በጣም ያሳዝነኛል።
ሰዎች እራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲቀበሉ ለመርዳት ብዙ መንገዶች ቢኖሩ እመኛለሁ። እንደ ኩዊር ክርስቲያን ራሴን መቀበሌ ሕይወቴን በጣም ለውጦታል። ከአሁን በኋላ ሀፍረት አይሰማኝም፣ እናም በእውነት ደስተኛ ነኝ። ሁሉም ሰው ይህን የሰላም ስሜት እንዲያገኝ እመኛለሁ።