በዚህ የሌዝቢያን ሳምንት ስለ ደስታ ማውራት እፈልጋለሁ። ህመምን ችላ የሚል የደስታ አይነት ግን አይደለም፤ ይልቅ በህመም ውስጥ ስለሚበቅለው ዓይነት ደስታ ነው።

እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የምኖር ሌዝቢያን ነኝ። ለዓመታት ራሴን እጠላ ነበር። ማህበረሰቡ ፍቅሬ ስህተት እንደሆነ አስተምሮኛል። ልቤን ከራሴ ደበቄ ኖሬያለሁ። ነገር ግን ቀስ በቀስ፣ ፍቅሬ ስህተት እንዳልሆነ ያሳዩኝን የኩዊር ቤተሰቤን አገኘሁ። እነሱም በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ፡ ሌዝቢያን ነኝ፣ እና በሌዝቢያንነቴም እኮራለሁ እንድል ረዱኝ።
“መታየት” ወይንም እራስን መግለጥ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሰው ሁሉ ስለ ማንነቴ መጮህ አይደለም። ለእኔ ታይነት ከውስጥ ነፃ መሆን ነው። መስታወት እያዩ ለራሴ “ሌዝቢያን ነኝ” ማለት ነው። ታሪኬን ለአንድ ታማኝ ጓደኛ ማካፈል ማለት ነው። የሄድኩበትን መንገድ ከሚረዱ ኩዊር እህቶቼ ጋር መደነስና በነፃነት መሳቅ ማለት ነው። እነዚህ ጥቃቅን ድርጊቶች የእኔ አመጽ እና ኩራት ናቸው።
ለኢትዮጵያውያን ኩዊር ቤተሰቤ፡- እዚህ መኖር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ። ሆሞፎቢያ ወይንም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጥላቻ ዙሪያችንን የከበበን ነገር ነው። ግን ስሙኝ – ደስታችን አስፈላጊ ነው። በድብቅ ስንሰበሰብ፣ ስንጠራራ፣ ውርደት እንዳያሸንፍ ስንታገል እኛ በፍቅር እና ተከብረን የምንኖርበትን ዓለም እንፈጥራለን። ኩራታችንን በአደባባይ ለማሳየት ገና ልንሆን እንችላለን፣ ነገር ግን በልባችን እና በግል ቦታዎቻችን ውስጥ፣ እኛ እራስችንን የምንገልጥ እና የምንታይ ነን።
በዚህ ሳምንት፣ በሁለት ነገሮች ላይ አተኩሬ ነበር፡-
1. ሕይወታችን ቀላል አይደለም
2. ደስታችን አሁንም ይቻላል
ኩዊር ኢትዮጵያውያን እርስበርስ የምንተሳሰብበት መንገድ ደስተኛ ያደርገኛል። በድብቅ ታሪኮቻችን የምንጋራበት መንገድ፣ “ብቻችን አይደለሽም” ለማለት የፈጠርናቸው ሚስጥራዊ ቋንቋዎች፣ ህመማችንን ወደ ጥበብ የለወጥንባቸው መንገዶች ያስደስቱኛል።
ትክክለኛ ማንነተችንን ለመሆን ለሁሉም ሰው ማንነታችንን መግለፅ አያስፈልግም። ታይነት በራስሽ ይጀምራል—የራስሽን ማንነት በልብሽ ለመናገር ድፍረት። ይህንን ለሚያነቡ ኩዊር ሰዎች፡- ኩራትሽ የአንቺ ነው፣ በማንኛውም ራስሽን አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ መግለጥ የምትችይው። ዓለም ባይቀበለንም እንኳ እራሱን የሚወድ ማህበረሰብ አካል ነሽ።
እለን። ሌዝቢያን፣ ኩዊር እና ማንም ከምንም ሊያቆመን የማይችል ብርቱ ሰዎች ነን። ደስታችንም ወደፊት መንገዳችንን ያሳምርልናል።