አንድም ጊዜ ለወንድ ልጅ አምርሬ ተስቤ አላውቅም። የውበት አድናቂ ስለሆንኩ ብቻ ቆንጆ ወንድ ደስ ይለኛል። በአንዳች ሱስ የተለከፍኩ ይመስል “ወደዚህ ህይወት መች ገባሽ? እንዴት ገባሽ?” እያሉ ይጠይቁኛል:: በርግጥ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ የቅርብ ጓደኛዬ የምላት ግን ሳልረዳው ያፈቀርኩዋት ሴት “lesbian ነኝ” ስትለኝ… ለመጀመሪያ ጊዜ የጠየኳት ጥያቄ ነበር:: እናም ልርቃት ወስኜ፤ መራቅን ጀመርኩ። የያዘኝ ፍቅሯ ግን አላራምድ አለኝ። ፍቅር መሆኑን ያልተረዳሁት እኔ ከዚህ ህይወት አወጣታለሁ ብዬ መልካም ጓደኝነታችን ቀጠለ ነገር ግን አልዘለቀም፣ ወደ ፍቅር ተቀየረ። ሁለታችንም በፍቅር እፍ አልን! የመጀመሪያም ከንፈሬን የሳመችኝ ሴት ሆነች።

አለማስተዋል ፣ ልጅነት እና የማህበረሰብ ነፀብራቅ መሆኔ እውነታውን እንዳልረዳ ጋረደኝ እንጂ ይሄን የሴት ፍቅር ተስቦዬን ማወቅ የነበረብኝ ገና ልጅ ሆኜ ነበር:: የ7ተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ አስተማሪያችን ከሌላ ግቢ የሆነችን ልጅ ከኛ ጋር ያስጠናትነበር:: በቁንጅናዋ ወንዱም ሴቱም አፉን ከፍቶ በየሚመሰክርላት ውብ ሴት!በፍቅር ስነሆልል፣ የጓደኝነት መውደድ ነው ብዬ ስጃጃል፣ ሁለቱ የቅርብ ጓደኞቼ እንደለመድኩት በፍቅሯ ስቆዝም አይተው “እሷን አትወጃትም ታፈቅሪያታለሽ እንጂ” ያሉኝ ጊዜ ነበር፤ ኧረ አናደውኝም ተጣልቻቸዋለሁ:: ለካስ እውነታቸውን ነበር! ከመውደድ በላይ የሆነ ስሜት ነበር የነበረኝ።
ታዲያ በ16 አመቴ ያቺ “lesbian ነኝ” ብላ ማንነቷን የገለጠችልኝ ሴት ወደህይወቴ መጥታ ማንነቴን አሳወቀችኝ:: ሴት ሆኜ ሴት አፍቃሪ መሆኔን እራሷን አፍቅሬ እንድረዳው አድርጋ አሳየችኝ። የፍቅር ጥያቄ እንኳን ከሷ ሳይሆን ከኔ ነበር የመጣው::
የፍቅሯ ሀያልነት ባህሌን ፣ ሀይማኖቴን ፣ የቤተሰቦቼን እና የማህበረሰቡን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያለ የተሳሳተ አመለካከት ሁሉ እንድተወው አደረገኝ። ሴት ሆኖ ሴት ማፍቀር ወይ ወንድ ሆኖ ወንድ ማፍቀር በጊዜ ሂደት የሚለቅ በሽታ ወይ ሱስ ሳይሆን ማንነት እንደሆነ አሳየችኝ። አሁን ምንም እንኳን አብረን ባንሆን ሁሌም የማመሰግናት ሴት ነች።