ዛሬ የኩራት ሰልፍ ተሰለፍኩ። በህልሜ ነበር፤ ግን በጣም እውን ሆኖ ተሰማኝ።

በጠዋቱ መስቀል አደባባይ ላይ መሰብሰብ ጀመርን። ፀሀይ ስትወጣ በሺህዎች የምንቆጠር ሆነናል። ጥለቱ የቀስተ ደመና የሆነ የሀበሻ ልብስ ለብሼ ነበር። ፍቅረኛዬ እጄን አጥብቃ ይዛኛለች። በጣም ጓጉተናል።
በሞተር ሳይክሎች ላይ ያሉ ሌዝቢያኖች የኩራት ሰልፉን ጀመሩ። በርካታ ሰዎች የኢትዮጵያ ባንዲራን እና ሌሎች ደግሞ ቀስተ ደመና ቀለም ያላችውን ባንዲራዎች ይዘው ይራመዱ ነበር። ሽማግሌዎች ባረኩን። ወጣቶች መንገዱን በሳቅና በዘፈን ሞሉት።
በቦሌ መንገድ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ስንሄድ አንድ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ። በመንገድ ዳር ያሉ ባለሱቆች እጃቸውን እያውለበለቡ በፈገግታ ሸኙን! አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ዳር ተቀምጠው አበረታቱን።
ምርጡ ነገር ሙዚቃው ነበር። በአገራችን ካሉ ክልሎች በሙሉ የተውጣጡ ሙዚቃዎች ጮክ ብለው ተጫውተዋል። እየሄድን ጨፈርን። ሁሉም ሰው ለቀድሞ ዘፈኖች አዲስ ቃላት ዘመረ፡- “ፍቅራችን እውነት ነው! አብረን ወደፊት እንራመዳለን!”
በሚሊኒየም አዳራሽ ትልቅ ድግስ ሆነ። ሙዚቃ፣ መጠጦች፣ ምግብ፣ ጣፋጮች፣ እና በጣም ብዙ ሰዎች እየጨፈሩ ነው። እናቶች በዚያን ጊዜ ፍቅር እንዲሰማቸው ለሚፈልጉ ሁሉ እቅፍ እያደረጉ “አይዞችሁ” አሉ።
ርችቶች የኩራት ቀኑ ማለቁን አበሰሩን።
እኔም ነቃሁ። ስካርፌ እንደገና ነጭ ነው። ህጉ አሁንም የኔን ፍቅርን ወንጀል ይለዋል። መንገዶቹ ጸጥ እንዳሉ ነው።
ግን ሕልሙ ከእኔ ጋር ይቆያል – የዘፈን ድምጽ፣ የፍቅረኛዬ እና የእኔ እጅ ለእጅ መያያዝ። ለዚያ የህልም ሰልፍ ማንም አልፈራም። ነፃ ነበርን። እራሳችንን ነበርን።
ይህ የኔ ጥልቅ ተስፋ ነው፡ አንድ ቀን ይህ ህልም ከልቤ ወጥቶ መስቀል አደባባይ ይደርሳል። እስከዚያ ድረስ ህልሜን አጥብቄ እይዛለሁ።