Skip to content Skip to footer

የኩራት ወር ድግስ

ወደ ፕሮግራሙ ቦታ መግባት ለማመን የሚከብድ ስሜት ነበረው ልክ እንደ ዳግም መገናኘት አይነት ስሜት ነበረው። ለዓመታት ያላየኃቸው ሰዎች እና ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ የማውቃቸው መሀል ነበርኩ። እንደ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳግም መገናኘት አይነት ነገር… ሁሉንም በግል ባታውቋቸውም ነገር ግን ታሪኮቻቸውን፣ ደስታቸውን፣ ጉዟቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተከታተላችኋቸው ስለሆነ የምታውቁት ቦታ አይነት ስሜት አለ አይደል? እንደዛ ነበር የተሰማኝ ።

“ፕሮግራሙ ማንነትን የሚያረጋግጥ እና የሚያረካ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር እና ለእኔ በቃ አለም ነበር። ከማንነቴ ውስጥ የትኛውንም ክፍል ሳላበላልጥ/ሳልደብቅ እና እራሴን ሙሉ በሙሉ ልሆን የምችልበት ቦታ ውስጥ መሆን በጣም ነፃነት ነበረው። ኩዊር የመሆንን ልዩ ልምድ ከሚረዱ ሌሎች ሀበሾች ጋር መገናኘት በጣም የሚያበረታታ ነበር። በጣም አስደሳች እንደነበረ ሳይዘነጋ! በሕይወቴ የማልረሳው ጊዜ ነበር፥ በእውነት!”

ከመቶ በላይ ኩዊር ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያን ነበርን። ከመላው የህብረተሰብ ክፍል የተሰባሰብን በኩዊርነታችን እና በኢትዮጵያዊ/ኤርትራዊ ማንነታችን አንድ የሆነን። ወጣት እና ጎልማሳ፣ ሀይማኖታዊ እና ሀይማኖታዊ ያልሆንን፣ አንዳንዶቻችን በማንነታችን ምክንያት የተሰደድን፣ እዚሁ የተወለዱ እና ሌሎች ለትምህርት ወይም ለደህንነት ወደዚህ የመጡ ነበሩ። ልዩነታችን ምንም ይሁን ምን አንድ ነገር አንድ አድርጎናል፥ ማህበረሰብ። የትውልድ አገሮቻችን ነፃነትን ቢነፍጉንም ሙሉ ማንነታችንን ለማክበር ያለን ፍላጎት እንደዚህ አገናኝቶናል። እንደእየማንነታችን ራሳችንን ሆነን ተገናኝተናል፣ በተለምዶ ወንዳወንድ የምንላቸው ሴቶች፣ በተለምዶ ሴታሴት የምንላቸው ወንዶች፣ ክሮስ ድሬሰርስ፣ እንዲሁም ከሁለትዮሽ ስርዓተ ጾታ ውጪ የሆኑ ቤተሰቦች ነበርን። እያንዳንዳችን በዚያ ክፍል ውስጥ ቦታ እና ደህንነትን አግኝተን ነበር።

“ፕሮግራሙ ባልጠበኩት መንገድ እንደ ቤት መመለስ አይነት ስሜት ነበረው። በሁለቱም ማንነቴ ፥ እንደ ሀበሻ እና እንደኩዊር ሙሉ በሙሉ ራሴን መሆን የቻልኩበት ቦታ ነበር።  ይሄንን አይነትን ቦታ ቀድሜ ባውቅ ወይም ቢኖር ኖሮ ብዬ ሳስብ ያማል፣ ነገር ግን በቦታው ተገኝቼ ምስክር መሆኔን ሳስብ ደግሞ ደስ ይላል።”

ባደግንበት ባህላዊ የቡና ስርአት ተከበን ተሸላለምን፤ ተመሰጋገንን ። እንጀራውን በተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪ ወንድ ጓደኞቻችን  በተዘጋጀው ወጥ አጣጣምን በላን። የሀገራችንን ሙዚቃ ያለፍርሀት እና ይቅርታ የኛው ነበር። እግራችን እስኪዝል ቤቱን በሞላው ባህላዊ ሙዚቃ ጨፈርን። ቀስተደመና ባንዲራን ልክ እንደነጠላ ከላያችን ወጥረን እስክስታ ወረድን። በጉራጊኛ ዘፈን እግሮቻችን አየር ላይ አወናጨፍን፣ ወገባችን በወላይታ ዘፈኖች አወዛወዝነው፣ በኦሮምኛ ዘፈን ወደላይ ዘለልን፣  በትግርኛ ዘፈን ክብ ሰርተን ተሽከረከርን።

“ኩራት ቆንጆ፣ አስደሳች፣ ስሜታዊ ተሞክሮ ነበር። ይህ ፕሮግራም ምን ያህል እንዳደገ ማየቴ ልቤን በብዙ ምስጋና እና ደስታ ይሞላዋል። ብቻችንን አለመሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው። በተለይም ብዙዎቻችን በሆነ ወቅት ላይ ብቸኝነት ተሰምቶን ያውቃል። የሚቀጥለው ፕሮግራም በጉጉት እጠብቃለሁ 💛😊”

ለእኔ ከበዓል በላይ ነበር። በእውነት ማንነትን በሚመቸን መተርጎም፣ የተቀማነውን እንደማስመለስ አይነት ነበር፤እንደመግለጫም፣ ፅናትን ማሳያም ነበር::

ውይይትም አድርገናል። እንዴት መቀጠል እንዳለብን፣ መገንባትን እንዴት መቀጠል እንዳለብን፣ እንቅስቃሴያችንን እንዴት ማጠናከር እንዳለብን ተነጋግረናል። ቃል ገብተናል፣ ራእዮችን ተጋርተናል፣ እና የበለጠ እና የተሻለ ለማሰብ መድፈር ችለናል። ከዛም ቀጥለን በሳቅ እና በደስታ እንባ፣ የቀስተ ደመና ኬክ ቆርጠን የኩራት ወርን በይፋ ተቀበልን።

“ማንነትን የሚያበረታታ እና አስደሳች ነበር! ለዜጋ ማህበር እና ለሁሉም የሀበሻ አዘጋጆች ምስጋናዬን በበቂ ሁኔታ መግለጽ የማልችል ሆኖ ይሰማኛል። የተገለሉ ማንነቶቼን መጋጠሚያ እንደማላገኝ በማመን እንደዚህ አይነት ማህበረሰብ ማግኘት አይቻልም ብዬ ብዙ አሳልፌያለሁ ስለዚህ እንደዚህ በአካል የመሰብሰብ እድሉ በጣም ልዩ ነበር። በሌሊቱ መገባደጃ ላይ፣ እኛ ምን ያህል ብዙ እንደሆንን እና ሁሉም ሰው ምን ያህል ልዩ እና አስደናቂ ነገሮችን እንዳከናወነ በማየቴ ለወደፊት ትልቅ ተስፋ ሰጥቶኛል::”

እስከሚቀጥለው አመት ድረስ፣ ልቤ በተቃውሞ፣ በፅናት፣ በተስፋ እና በፍቅር ዜማዎች መደነሷን ትቀጥላለች።

እንኳን ደስ አለን። ፍቅር በእውነት አሸነፏል።

Leave a Reply

Discover more from queerethiopia

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading